Mobile menu

የሴክተሩ ገጽታ

 

 

የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ንዑስ ዘርፍ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለመውጥ የጀርባ አጥንት ነው!


የአገራችን የህዳሴ ጉዞና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማሳለጥና የተጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ንዑስ ዘርፍ ልማት ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ይህንን አገራዊ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚያስችል “አገራችን በ2017 በአፍሪካ ቀዳሚ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ቀላል የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ በመገንባት፣ ለከባድ ኢንዱስትሪ  ልማት መሠረት መጣል” በሚል ራዕይ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡


መንግሥት በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ተመጣጣኝ የማበረታቻ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንቱ እንዲስፋፋም ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ በሁሉም ዘርፎች ማለትም በአርማታ፣ በስቲልና ፕሮፋይል፣በማሽነሪና ኢኩዩፕመንት፣ በአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ፣ በአሉሙኒየም ፕሮፋይል፣ በኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪካል ኢንቨስትመንት ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎች ከ400 በላይ ሲሆኑ፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች 85 በመቶውን  ሲሸፍኑ ቀሪው 15 በመቶ ደግሞ በውጭ ኩባንያዎችና በሽርክና የተያዙ ናቸው፡፡


ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለቀላቸው ጥሬ ዕቃዎችን በማስገባትና እሴት በመጨመር የግንባታ ዕቃዎች ለማምረት የተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች ዕድገት አሳይተዋል፡፡ የዜጎች የነፍስ ወከፍ የብረት ፍጆታ በመጀመሪያው ዕትዕ ዘመን ከነበረው 12 ኪሎ ግራም ገደማ ወደ 39 ኪሎ ግራም ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ የአቅም አጠቃቀምም በሚፈለገው ፍጥነት ባይሆንም መሻሻሎች አሉ፡፡


የብረት ማዕድናትን በማልማት ለአገር ውስጥ ምርት መጠቀም ቁመና ላይ ያልተደረሰ ቢሆንም ያለውን ውስን የውድቅዳቂ ብረታ ብረቶችን ተጠቅሞ የአርማታ ብረት፣ የአሉሚኒየም፣ የኮፐር፣ የኤልክትሪክና የቴሌኮም ኬብሎችን የሚያመርቱና የአገሪቱን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች በመፈጠራቸው በግብአት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተቀርፏል፡፡


ብረቶችን በማቅጠን ለግንባታና ለፋብሪኬሽን የሚረዳ ጠፍጣፋ ቆርቆሮዎችና ብረቶችን ማምረት ተችሏል፡፡ የቶቦላሬ ምርቶችን በአገር ውስጥ አቅም በመተካት እየተካሄድ ላለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ልማት ግብአት የሚሆን በማቅረብ ረገድ በአገር ውስጥ አቅም መሸፈን የሚቻልበት ደረጃ እየተደረሰ ነው፡፡ ለማሳያነትም 1.6 ሚሊዮን ቶን በላይ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት የሚችሉ የኢንዱስትሪዎች አቅም ተፈጥሯል፡፡


ትኩረት ለተሰጣቸው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ቆዳ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ምግብና መጠጥና ኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ማሽነሪዎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም ፍላጎቶች በግሉ ባለሀብትም ሆነ ከሌሎች ጋር በቅንጅት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎችንም ፕሮሰስ ፕላኖቶች በአገር ውስጥ አቅም የማስፋፋት ጥረቶችም በሂደት ላይ ናቸው፡፡


ለስኳር ኢንዱስትሪዎች ግንባታም ኮምፖኔንቶችን ከ70-80 በመቶ በራስ አቅም ማምረት መቻሉ፣ በዓመት እስከ 1,000 የሚደርስ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን መገጣጠም አቅም የተፈጠረ መሆኑና እስከ 5,000 ገደማ የእርሻ መሳሪያዎችን ወይም ትራክተሮችንና 4,000 የሚደርሱ ተቀጥላዎቻቸውን በአገር ውስጥ የማምረት አቅም መፈጠሩ የዕትዕ ግቦች ስኬት ማሳያዎች ናቸው፡፡


አውቶሞቲቪና ሌሎች ተሸከርካሪዎችን በመገጣጠም፣ የጭነት ተሸከሪካሪዎችን አካላትና ተጎታቾቻውን እንዲሁም የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አካላት በአገር ውስጥ በመፈበረክና በመገጣጠም የሎጂስቲክስ ወጪን ከመቀነስ በተጨማሪ የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅም እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡


የኤሌክትሪክ ትራንስፎርሜሮችን የኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያና የማከፋፈያ ቦርዶችና ኢኩዩፒመንቶችን፣ ባትሪዎችንና ሃይል የሚያጠራቅሙ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኬብሎችን በማምረት ገቢ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ የመተካት አቅም ተፈጥሯል፡፡ የቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ ማብሰያዎችን፣ ማሞቅያዎችና ሌሎች ኢኩዩፒመንት በከፍተኛ አቅም ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ መፈጠራቸው ገቢ ምርቶችን ለመተካት የተደረጉ ጥረቶች አካል ናቸው፡፡


አገራዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የግል ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችና የህብረተሰብ ፍላጎት ለማሟላት የ2009 በጀት ዓመት ፍላጎት 3.355 ሚሊዮን ቶን ገደማ የደረሰ ሲሆን በንዑስ ዘርፉ በማምረት ተግባር ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ሙሉ አቅማቸውን ማምረት ሲጀምሩ እና በፕጀክት ላይ ያሉ ወደ ማምረት ከተሸጋገሩ 3.669 ሚሊዮን ቶን በዓመት ማምረት ይቻላል፡፡ ይህም የገቢ ምርት ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ መሸፈን ይችላል፡፡


ከመጀመሪያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ጀምሮ ገቢ ምርቶችን ከመተካት በተጨማሪ በተወሰኑ የምርት ዘርፎች ወጪ ንግድ ላይ በጥራት፣ በዋጋና አቅርቦት ተወዳዳሪ ሆኖ ለገበያ መቅረብ የሚያስችል እንቅስቃሴም ተደርጓል፡፡ በ2006     በጀትዓመት 3,189,000.02  አሜሪካ ዶላር የተጀመረው የወጪ ንግድ በ2007 በጀት ዓመት 14,943,000.49፣ በ2008 በጀት ዓመት 22,055,133.81 እና በ2009 የዘጠኝ ወራት 20,923,003.01 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ወደ ውጭ መላክ ተችሏል፡፡


በመሆኑም የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ንዑስ ዘርፍ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለንዑስ ዘርፉ ልማትና ዕድገት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ያደጉ አገራትም የማደጋቸው ሚስጢር ከሆኑት ጉዳዮች መካካል አንዱ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪግ ልማት ዘርፍ ነውና!